ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሂደት የተመለከተ ውይይት ነገ ይካሄዳል፤

Image may contain: sky and outdoor
FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)

34 mins

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሂደት የተመለከተ እና “ግድቡ የኔ ነው’’ በሚል መሪ ቃል ነገ የበይነ መረብ ውይይት እንደሚካሄድ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።

ኤምባሲው ዛሬ እንዳስታወቀው በውይይቱ በደቡብ አፍሪካና ኤምባሲው በተወከለባቸው ሰባት ሃገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በመላው ዓለም ኢትዮጵያን የሚወክሉ ሚሲዮኖች፣ ስመጥር ምሁራንና ባለሀብቶች ተሳታፊ ይሆናሉ።

በውይይቱ ግድቡ ያለፈበት ሂደት እና አሁን የደረሰበት ደረጃ፣ የግብጽ ጫና እና የድርድሩ ሂደት ያለበት ሁኔታ፣ በግድቡ አጠቃላይ ሂደት ላይ የመንግስት አቋም፣ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች፣ በቀጣይ በውጭ ሃገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ
ገንቢ አስተዋጽኦ እና በሌሎች መሰል ጉዳዮች ላይ አስተያየት ቀርቦ ምላሽና ማብራሪያ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

በውይይቱ የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ በሚደረጉ ድርድሮች ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው የሃገራችን ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት እና በዘርፉ የጠለቀ ዕውቀትና ልምድ ያካበቱ ምሁራን ከሃገር ቤት እና ከውጭ ሃገራት ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡

በውይይቱ ለመሳተፍ ከ400 በላይ ተሳታፊዎች የተመዘገቡ ሲሆን ሂደቱ በኤምባሲው እና በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ማህበራዊ ሚዲያዎች በቀጥታ እንዲሁም በሀገር ቤት መገናኛ ብዙሃንም ሽፋን እንደሚሰጠው ታውቋል።

ውይይቱ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲና በደቡባዊ አፍሪካ በሚገኝ የኢትዮጵያውያን ምሁራን ማህበር ትብብር ውይይቱ በጋራ የተዘጋጀ ነው።

Posted in News.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *