አሜሪካ በመድሎ ከያዘችው የግድቡ ድርድር ገለል ብላ ለእውነተኛ ድርድር ድጋፍ እንድታደርግ የሀገሪቱ የቀድሞ ባለስልጣናት አሳሰቡ

Image may contain: 5 people, closeup
FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)

2 hrs

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አሜሪካ በመድሎ ከያዘችው የግድቡ ድርድር ገለል ብላ ለእውነተኛ ድርድር ድጋፍ እንድታደርግ የሀገሪቱ የቀድሞ ባለስልጣናት አሳሰቡ።

ባለስልጣናቱ በጉዳዩ ላይ ሀገራቸው ገለልተኛ እንድትሆንና ግልጽና ፍትሃዊ የሽምግልና ሂደትን እንድትከተል ነው የጠየቁት።

አምባሳደር ሱዛን ራይስ፣ አምባሳደር ጀንዳይ ፍሬዘር እና አምባሳደር ሄርማን ኮሆንን ጨምሮ ሰባት የቀድሞ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በጻፉት ደብዳቤ አሁን ላይ ግድቡ ላይ እየተካሄዱ ያሉ ውይይቶች ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሳቸውን አንስተዋል።

ከዚህ አንጻርም ዋሽንግተን ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ በገለልተኝነት ልትንቀሳቀስ ይገባታል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ሃገራቸው ግልጽና ፍትሃዊ የሽምግልና ሂደትን የተከተለ አካሄድ ሊኖራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

አምባሳደሮቹ አሜሪካ አውቃም ይሁን በስህተት ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ ለግብጽ መወገኗ በጉዳዩ ላይ ለመድረስ ለታሰበው ስምምነት በምታደርገው ጥረት ላይ ሚናዋን እንደሚገድበውም አስገንዝበዋል።

ከዚህ ባለፈም ከግድቡ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማድረግም ሆነ የሚደረጉ ድጋፎችን ማገድ ጉዳዩን አስቸጋሪ ከማድረጉም በላይ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚደረገውን ጥረት አስቻገሪ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል።

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ኢትዮጵያ እና ግብፅን እንዲያደራድሩ በደብዳቤያቸው የጠየቁት የአሜሪካ የቀድሞ ከፍተኛ ባለሰልጣናት፥ ዩናይትድ ስቴትስ በግድቡ ላይ እየተካሄደ ካለው ድርድር ገለል እንድትል፣ አደራዳሪዎች በራሳቸው መፍትሄ እንዲፈልጉ እንድታደርግ እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ ድርድር ይፋዊ ድጋፏን እንድትሰጥም አሳስበዋል።

ሱዳን ከኢትዮጵያ እና ግብፅ ጋር ያላትን ግንኙነት ሚዛን ጠብቃ ለመሄድ በምታደርገው ጥረት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች የጠቆሙት ባለስልጣናቱ ፥ ሆኖም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መፍትሄ ለመፈለግ ግን የተሻለ ቦታ ላይ እንደምትገኝ ነው ያመለከቱት።

አሁን በግድቡ ላይ አሜሪካ የያዘችው ገለልተኛ ያልሆነ እና ለግብፅ ያዳላ አቋም በሱዳንም በጦሩ እና በሲቪል አስተዳደሩ መካከል ክፍተት በመፍጠር የሀገሪቱን ሽግግር በማደናቀፍ ሰላምን የሚያናጋ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።

ይህን አለመግባባት ለመፍታት አሜሪካ ከአፍሪካ እና ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ውጪ የሆነ ገለልተኛ ሀገር እንዲሳተፍ ልታበረታታ ይገባታልም ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ወሳኝ ምእራፍ ላይ መግባቱን የጠቆሙት ባለስልጣናቱ፥ የአሜሪካ ብሄራዊ ጥቅም እንዲጠበቅ፣ በአካባቢው ፀጥታና እና መረጋጋት እንዲሰፍን አሜሪካ በዚህ ሂደት ውስጥ ገለልተኛ እንድትሆን እና እውነተኛ ድርድር እንዲካሄድ እንድትደግፍ ነው ያሳሰቡት።

Posted in News.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *